Thursday, December 5, 2013

‹‹መለስ ዛሬ የለም፡፡ አዲስ ጊዜ ነው፡፡ ደስ ብሎኛል፤ ቪዛዬም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተሰጥቶኛል፡፡››...አና ጎሜዝ

Decenber 5/2013

የሸፈተው የአና ጎሜዝ ልብ?!

‹‹መለስ ዛሬ የለም፡፡ አዲስ ጊዜ ነው፡፡ ደስ ብሎኛል፤ ቪዛዬም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተሰጥቶኛል፡፡››...
(… Meles has gone! This is a new timing. I am pleased I was granted visa without preconditions.)
ይህንን ያሉት በምርጫ በ1997 የአውሮፓ ኅብረት ምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ ሆነው የመጡት ሚስስ አና ጎሜዝ ሰሞኑን ከአዲስ ስታንዳርድ መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነው፡፡
የአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ መሰንበቻውን ካስተናግደችው ጉባኤዎች መካከል የአፍሪካ ካሪቢያን፣ የፓስፊክና አውሮፓ የጋራ የፓርላማ ስብሰባ አንዱ ነበር፡፡ ጉባኤው የመንግሥት ሚዲያ ቀልብ ይሳብ እንጂ የሕዝቡን ቀልብ የሳበው ግን ሌላ ነው፡፡ ሪፖርተርን ጨምሮ የግሉን ሚዲያና የሕዝቡን ቀልብ የሳበው የሚስስ አና ጎሜዝ ወደ አዲስ አበባ መምጣት ነው፡፡ 
ከዘጠኝ ዓመት በፊት ከመንግሥት ጋር የተወዛገቡት የአና ጎሜዝ መምጣት የበለጠ አስገራሚ ያደረገው እሳቸው በዚሁ ጉባኤ በአዲስ አበባ መገኘታቸው ብቻ አይመስልም፡፡ እሳቸው በአባልነታቸው የሚታወቁበት አውሮፓ ኅብረት ፓርላማ ለኢትዮጵያ 5.5 ቢሊዮን ብር በዕርዳታ መልክ መለገሱን ኢቲቪ ዘግቧል፡፡ በአመዛኙ የምርጫ 97ን ተከትሎ የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበቡን ቢናገሩም፤ ከአንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ግልጽ ውይይት ማድረጋቸውና አዲስ የለውጥ ነፋስ አየሁ ማለታቸውም ሌላው አነጋጋሪ አጀንዳ ሆኗል፡፡ 
አና ጎሜዝና ምርጫ 97
ኢትዮጵያ ከደርግ ውድቀት በኋላ ቢያንስ በመርህ ደረጃ የሕዝብ ይሁንታ የሚረጋገጥበት ሕዝባዊ ሥልጣን በምርጫ የሚያዝበት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ታውጇል፡፡ ኢሕአዴግ አብዛኛው የፓርላማ መቀመጫውን በምርጫ ስም (ገለልተኛ ታዛቢዎች እንደሚሉት) መቆጣጠር ይዞት የመጣው ባህል፣ በሦስተኛው ዙር የ1997ቱ አገራዊ ምርጫ ተሰብሮ ነበር፡፡ በወቅቱ እንደ አሸን የፈሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁለት አውራ ጥምረቶች (ኅብረትና ቅንጅት) በመፍጠር ገዥውን ፓርቲ ኢሕአዴግ በሰላማዊ መንገድ መፈታተን ችለው ነበር፡፡ ኋላ ኋላ ጉዳዩ ላይ ጥናት ያካሄዱት ምሁራን እንደሚሉት በሙያ ሥነ ምግባር ጉድለት ምክንያት፣ የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨት አደገኛነቱ የሚያመዝን ቢሆንም፣ የግል ሚዲያው በአገሪቱ ታሪክ ተጠናክሮ የመጣበት ወቅትም ነበር፡፡ መንግሥት የሰነዘራቸው ከፍተኛ ትችቶች ሳይዘነጉም የአገር በቀልና የውጭ ሲቪክ ማኅበራትም በፖለቲካው የላቀ ሚናቸውን ተጫውተዋል፡፡  
ይኸው የ97ቱ ምርጫ በአንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍል ላይ የራሱ የሆነ የማይረሳ መጥፎ ጠባሳ ጥሎ አልፏል፡፡ በመንግሥትና በተቃዋሚዎች ግንኙነት ላይ ያስከተለው ሕመምም አሁንም ድረስ አልተፈወሰም፡፡ ምርጫውን ተከትሎ ለተፈጠረው ቀውስም፣ በዋና ተዋናዮቹ ሁለቱ ወገኖች ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ 
ኢሕአዴግ እንደሚለው፣ አንዳንድ የፖለቲካ ሰዎች የራሳቸው የፖለቲካ አጀንዳ ይዘው የተንቀሳቀሱ የ‹‹ኒዮሊበራል›› ኃይሎች በገንዘብም ሆነ በሞራል ጫና ለመፍጠር ክፍተቱን ተጠቅመው ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ይህ በማናቸውም አገሮች የሚፈጠር ቀውስ ለውጭ ኃይሎች በር መክፈቱ ግን በኢትዮጵያም በሌሎች አገሮችም እንግዳ አይደለም፡፡ በምርጫም ሽፋንም ሆነ በኃይል በመፈንቅለ መንግሥት፣ በተለይ ምዕራባውያን ኃይሎች የማይፈልጉትን አካል ለመጣልና የሚፈልጉትን ወገን ደግሞ ለማንገሥ ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ ጣልቃ ገብነት ከማድረግ አይቦዝኑም፡፡ የሚያስከትለው ውጤት ከአገር አገር ይለይ እንጂ፣ በተለይ በድሀ አፍሪካ አገሮች የእነዚህ ኃይሎች እጅ ረዘም ያለ ነበር፡፡ ዋና አጀንዳቸው ባይሆንም ለዲሞክራሲ መስፋፋት ምንም ዓይነት ፋይዳ አይኖራቸውም ግን አይባልም፡፡ 
ከምርጫ 97 ጋር በተያያዘ ስማቸው በቀላሉ ከሕዝብ አእምሮ ከማይጠፋው ጥቂት የፖለቲካ ሰዎች እኩል የሚታየው፣ የውጭ ሰዎች ግንባር ቀደሙ ደግሞ የሚስስ አና ጎሜዝ ነው፡፡ ለዚህም ይሆናል ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተደረገው ዓለም አቀፍ ጉባኤና ከአውሮፓ ኅብረት ከፍተኛ ዕርዳታም በላይ፣ የብዙዎችን ቀልብ የሳበ የሚመስለው፡፡ ወይዘሮዋ በአሁኑ ወቅት በተለይ የአዲስ አበባን ነዋሪዎች ቀልብ የሳቡት ከምርጫው ቀውስ ዘጠኝ ዓመት በኋላ ወደ ከተማይቱ ሲመጡ ለመጀመርያ ጊዜ በመሆኑ ብቻ አይመስልም፡፡ ያሳዩት የአቋም ለውጥ ጭምር እንጂ፡፡ 
የአና ጎሜዝ ልብ ዛሬ ወዴት ነው?
ከሁለት ዓመት እስር በኋላ በይቅርታ የተፈቱ የቅንጅት አመራሮች፣ የሚዲያና የሲቪክ ማኅበራት የፖለቲካ አራማጆችም፣ በምርጫው ወቅት ያሳዩትን ጉልበት ይዘው መቀጠል አልቻሉም፡፡ በተቃዋሚዎች ላይ ተስፋ የቆረጡት ግን የአሜሪካ መንግሥት (ቀጥሎ የመጣው የኦባማ አስተዳደር) እና የአውሮፓ ኅብረት ብቻ አልነበሩም፡፡ በምርጫ ውጤት እንደታየው፣ መራጩ ሕዝብ በተቃዋሚዎች ላይ ተስፋ መቁረጡን በግልጽ አሳይቷል፡፡ ማሳያው በ1997 ምርጫ መቶ በመቶ ቅንጅትን የመረጠው የአዲስ አበባው ሕዝብ፣ ከአንድ ወንበር በስተቀር በ2002 ዓ.ም. ኢሕአዴግን መርጧል፡፡ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት፣ የፖለቲካ ቁርጠኝነት የትግል ጽናት የላቸውም ብሎ ተስፋ የቆረጠባቸው የተቃዋሚዎች አመራሮች ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ተንቀሳቅሰናል›› በሚል ይቅርታ መጠየቃቸው ብቻም አይመስልም፡፡ መሪዎቹ ከእስር ከወጡ በኋላ በሁለት እግሩ መቆም የሚችል ድርጅት ይዘው መቀጠል አለመቻላቸውም ጭምር ነው፡፡ ይህንን በማድረግ ምትክ፣ በመካከላቸው በተፈጠረው አለመግባባት ወደተራ ድብድብ እስከመግባት የደረሱ ነበሩ፡፡ መንግሥት ይህንን ክስተት ለፕሮፖጋንዳ በስፋት ተጠቅሞት ነበር፡፡ 
በቅርቡ አዲስ አበባ የመጡት አና ጎሜዝ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተው ግልጽ የሆነ ውይይት ማድረጋቸው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ከተቃዋሚዎች ጋር ምንም ንግግር አለማድረጋቸው ይነገራል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ድንገተኛ ሕልፈት አገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር እንድታደርግ እንደ መልካም አጋጣሚ የተመለከቱት አና ጎሜዝ፣ በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ መሠረታዊ የሆነ ለውጥ ለማየት የጓጉ ይመስላሉ፡፡ 
በዚሁ ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፣ ‹‹አዲስ ነፋስ አለ›› ያሉት መንግሥት ለእሳቸው ያለምንም መንገላታትና እንቅፋት ቪዛ ስለሰጣቸው የአወንታዊው ለውጥ ምልከታቸው ቀዳሚ ነው፡፡ አሁንም ከ97 በኋላ የፖለቲካ ምህዳሩን በተመለከተ ችግሮች መኖራቸው አስረግጠው የተናገሩት አና ጎሜዝ፣ በአጠቃላይ ግን አገሪቱ በተለየና አዲስ አመራር ውስጥ መሆኗን ይናገራሉ፡፡ ያዩዋቸው ለውጦች ምን ምን እንደሚያካትቱ በዝርዝር ባያስረዱም፡፡ አንድ ትልቅ ለውጥ የተመለከቱት የሶሻል ሚዲያ መስፋፋት ሲሆን፣ ያንንም ከመንግሥት ቁጥጥር በላይ በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡ በሙሰኞች ላይ የተወሰደ ዕርምጃም አድንቀዋል፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ ላይ እኔ ምንም የኢኮኖሚ ሆነ ምንም ግላዊ ፍላጎት የለኝም›› የሚሉት አና ጎሜዝ፣ አንዳንድ ባለሥልጣናት በግልጽ ለመነጋገር መፍቀዳቸውንም እንደ ለውጥ ሳይመለከቱት አልቀሩም፡፡ ‹‹እኔን ለመስማት መፈለጋቸው ራሱ ጥሩ ይመስለኛል›› ብለዋል፡፡ ‹‹በሽብርተኝነት የታሠሩት ጋዜጠኞች እንጂ አሸባሪዎች አይደሉም›› ለሚለው ሙግታቸው ማስረጃ እንዲያቀርቡ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ‹‹ጋዜጠኞች መሆናቸውን ነው የማውቀው›› ከማለት ውጪ የማቀርበው ማስረጃም የለኝም ብለዋል፡፡ 
በወቅቱ ከቅንጅት አመራሮች አንዱ የነበሩት ዶክተር ኃይሉ አርአያ፣ የአና ጎሜዝን መምጣት በበጎ ጎን አይተውታል፡፡ ‹‹መቀራረቡ በእኔ በኩል ገንቢ ነገር ነው፤››  የሚሉት ዶክተር ኃይሉ፣ ‹‹በአገሪቱ ተለውጧል ያሉትን ነገር ግን እሳቸው ብቻ ናቸው የሚያውቁት፡፡ እሳቸው በወቅቱ ይዘውት ከነበረው አቋም አሁን ምንም የተለወጠ ነገር አላየሁም፡፡ አቋማቸውን የሚያስለውጥ መሠረታዊ ለውጥ አላየሁም፤›› ብለዋል፡፡ ዶክተር ኃይሉ እንደሚሉት፣ በአገሪቱ እሳቸውም የማይክዱት ልማት እየመጣ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ከዚያ ውጪ ግን በፖለቲካ መስክ ምንም የመጣ ለውጥ የለም፡፡ ቪዛ ስለተሰጣቸው ብቻ አዲስ ለውጥ አለ ማለት ግን አግባብ አይደለም፤›› ይላሉ፡፡ 
የቀድሞ አምባሳደር ተስፋዬ ሀቢሶ በበኩላቸው በ1997 ዓ.ም. በካምፓላ (ኡጋንዳ) አምባሳደር የነበሩ ቢሆንም ጉዳዩን በቅርበት ይከታተሉ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ አና ጎሜዝ በወቅቱ በኢትዮጵያ ላይ የያዙት አቋም የግላቸው እንዳልነበር በአጠቃላይ የምዕራባውያን መንግሥታት አቋም እንደነበር ይናገራሉ፡፡ በተለይ ደግሞ፣ ኒዮሊበራሊዝምን አክርረው የሚቃወሙት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስን እንደ ‹‹የወገብ ቅማል›› አድርገው ነበር የሚያዩዋቸው ብለዋል፡፡ በወቅቱ ከኢትዮጵያ የተባረሩት አራት የውጭ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችም የተቃውሞ እንቅስቃሴውን በገንዘብ ሲደግፉ እንደነበር ለአብነት ይጠቅሳሉ፡፡ አና ጎሜዝ ብቻም ሳይሆኑ እነ ክርስቶፈር ክላፋም፣ ክሪስ ቦርና የኤችአር 2003 ሕግ አርቃቂ ዶናልድ ፐይን የመሳሰሉትም በተመሳሳይ ይጠቅሳሉ፡፡ እሳቸውም እንደ ዶክተር ኃይሉ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ አቋም የሚያስለውጥ ምንም የተለወጠ ነገር የለም፤›› በሚለው ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ 
አና ጎሜዝ ከመንግሥት ጋር መታረቅ የፈለጉበት ምክንያት ግን ‹‹ታክቲክ›› እንደሚሆን በመገመት፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ ላይ ያለው አቋም መለወጡን ተስፋ እንዳስቆረጣቸው ይገምታሉ፡፡ ‹‹ከወደቀ ጋር መሆን ማን ይፈልጋል?›› በማለት፡፡ ‹‹አሁን በ60 ዲግሪ አቋማቸው ተለውጧል ያሉት አምባሳደር ተስፋዬ፣ ግለሰቦች የራሳቸው ሚና ቢኖራቸውም ያው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የተዉት ፖሊሲና ርዕዮተ ዓለም እየተተገበረ ስለሆነ ምንም አቋም የሚያስለውጥ ነገር የለም፤›› ይላሉ፡፡ ‹‹ስህተታቸውን አምነው፣ ለውጡ ከልብ ተቀብለውት ከሆነ ግን መልካሙን እመኝላቸዋለሁ›› ብለዋል፡፡ 
በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሰላምና ልማት ተቋም ተመራማሪው አቶ አቤል አባተ በበኩላቸው፣ ‹‹የአና ጎሜዝ መለሳለስ ከአውሮፓ ውስጥ የደረሰባቸው መገለል ውጤት ነው፤›› ይላሉ፡፡ ከ1997 ምርጫ በኋላ የኢሕአዴግ መጠናከርና መንግሥት በልማት ላይ ያሳያቸው ተጨባጭ ዕድገቶች የተቺዎቹን አፍ እየዘጋለት እንደሆነ በመግለጽ፡፡ ለዚህም ከአቶ መለስ ሕልፈት በኋላ ምንም ዓይነት የፖሊሲም ሆነ የስትራቴጂ ለውጥ ባልታየበት የአና ጎሜዝ መለሳለስ ጥሩ ማሳያ ነው ብለውታል፡፡ 
‹‹ቀደም ሲል ከተቃዋሚ አመራሮች ጋር የነበራቸው መጥፎ ስም ለማደስ ፈልገው ይሆናል፡፡ ለአቋማቸው መለወጥ ዋነኛ ምክንያት ግን መገለላቸውና በአውሮፓ ኅብረት ውስጥ ምንም ዓይነት ተሰሚነትና ተአማኒነት ማጣታቸው ነው፡፡›› 
የባከኑ ስምንት ዓመታት
አና ጎሜዝ ሰሞኑን እዚሁ አዲስ አበባ እስከታዩ ድረስ፣ በተገኙ አጋጣሚዎች በሙሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ሲከሱ፣ ሲወነጅሉና ሲያጣጥሉ ቆይተዋል፡፡ 
ከይቅርታ ጠያቂዎቹ መካከል ወደ አሜሪካና አውሮፓ የገቡ አንዳንድ አመራሮች ከውጭ በመሆን ከእነ ሚስስ አና ጎሜዝና ዶናልድ ፔይን (ከሦስት ዓመት በፊት ሕይወታቸው ያለፈው) ጋር በመሆን ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡ መንግሥትን በኃይል ለመጣል ከዳያስፖራ ድጋፍ እያሰባሰበ የሚገኘውና በመንግሥት በአሸባሪነት የተፈረጀው ግንቦት ሰባት ሊቀመንበሩ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ (በአገር ክህደት ክስ በሌሉበት ሞት የተፈረደባቸው) ጋር በቅርበት ሲሠሩ ከቆዩት መካከል፣ አሁን ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ‹‹ግልፅ›› ውይይት ማድረጋቸውን የሚናገሩት ሚስስ አና ጎሜዝ ናቸው፡፡ በአውሮፓ ኅብረት አስተባባሪነት ኢትዮጵያን በሚመለከቱ መድረኮች፣ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ የተለያዩ ተቃውሞአቸውን እንዲገልጹም ከማመቻቸት ባሻገር ራሳቸው በተለያዩ ወቅቶች ኅብረቱ በኢትዮጵያ ላይ እንዲጨክን ድምፃቸውን ሲያሰሙ ኑረዋል፡፡ በኢትዮጵያ በሽብርተኝነት ክስ ተፈርዶባቸው በእስር የሚገኙት ግለሰቦች በአስቸኳይ እንዲፈቱ፣ መንግሥት ያፀደቃቸውን ሕጎች እንዲከልስ፣ ኅብረቱ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ዕርዳታም ሆነ ብድር እንዲያቋርጥ በተለያዩ መንገዶች ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ የእሳቸው ጥረት፣ በአጠቃላይ የአውሮፓ ኅብረትና አባል አገሮች ሥልጣን ላይ ባለው መንግሥት ዕውቅና እንዲነፍጉ የሚጠይቅ ነው፡፡ ከዚያም አልፈው ወይዘሮዋ፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ባለው የድንበር ግጭትም ጭምር አስተያየት የሚሰጡ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሄጉ ፍርደ ገምድል ውሳኔ ተፈጻሚ እንዲያደርግ ለዚህም ኅብረቱ ጫና እንዲፈጥር ይጠይቃሉ፡፡ 
በተለይ አምና መጋቢት ወር ላይ ለኅብረቱ ባቀረቡት ስሞታ፣ የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የሆኑት ጆሴ ማኑኤል ባሮሶ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን በሚያነጋግሩዋቸው ወቅት፣ አገሪቱ ‹‹የፖለቲካ›› እስረኞቿን በአስቸኳይ እንድትፈታ የድንበር ውሳኔው በአስቸኳይ እንዲተገበርና በሶማሊያ የምታደርገውን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እንድታቆም ጫና እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹በእርግጥ እሳቸው ማምጣት የሚችሉት ለውጥ እምብዛም ነው›› ያሉዋቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምንም የሥልጣን ሽግግር እንዲያደርጉ ፕሬዚዳንቱ ጫና ይፈጥሩ ዘንድ ተማጽነው ነበር፡፡ አውሮፓ ኅብረት ምርጫ 97ን ተከትሎ ያደረገው ለውጥ ካለ፣ ለአገሪቱ የሚሰጠው ዕርዳታ በመንግሥት በኩል መሆኑ ቀርቶ በፕሮጀክቶች አማካይነት በቀጥታ ለዜጎች እንዲውል ማድረጉ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ በሶማሊያም ጉዳይ ሆነ በአካባቢው ደኅንነትና የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ትብብሮች ዙርያ በጋራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ይህ ግን ለአና ጎሜዝ ፍፁም ተቀባይነት የለውም፡፡ ኅብረቱ በኢትዮጵያ ላይ የሚከተለው ፖሊሲ እስካሁንም አይዋጥላቸውም፡፡
በመጀመርያ አካባቢ የአውሮፓ ኅብረት በተለይ ደግሞ የኅብረቱ ዋና አከርካሪ ከሆኑት አባል አገሮች ግንባር ቀደም ከሆኑት መካከል እንግሊዝ በኢትዮጵያ ላይ የዕርዳታና ብድር ለኢትዮጵያ መንግሥት በቀጥታ እንዳይሰጥ በመከልከል የተሳካላት ቢመስልም የኋላ ኋላ ነገሮች እየተቀየሩ መጥተዋል፡፡ የአውሮፓ ኅብረትም ሆነ የአሜሪካ መንግሥት፣ ተስፋ የጣለባቸው ተቃዋሚዎችና ‹‹አክቲቪስቶች›› ወደ እስር ቤት በመግባታቸው ተፅዕኖዋቸው እየቀጨጨ በመሄዱ የውጭ ኃይሎችም ተስፋ እየቆረጡ መጥተዋል፡፡ ወይዘሮዋም ‹‹አይዟችሁ›› ሲሉዋቸው የነበሩ አመራሮችን ከእስር አላዳኑዋቸውም፡፡ 
እንደ የፖለቲካ ተመራማሪዎች ትንተና፣ በአገሪቱ የተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስና መንግሥት የሰጠው አሉታዊ ምላሽ፣ የአገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ጉዞን ወደ ኋላ እንዲያፈገፍግ ምክንያት ቢሆንም፣ የውጭ ኃይሎች ግን ተስፋ የተጣለውን ያህል ተቃዋሚዎች የዲሞክራሲ ጉዞውንም የሚታደጉ አልነበሩም፡፡ ከውጭ ተፅዕኖ በአንጻራዊነት ነፃ መሆኑን የሚያምነው ኢሕአዴግም ሊቀመንበሩ አቶ መለስም፣ ክፍተቱን ተጠቅመው በኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን የሰደዱ ኃይሎች በቀላሉ መቋቋም ችለዋል፡፡ 
የአና ጎሜዝ ድምዳሜና መዘዙ
የመለስ ዜናዊ አጠቃላይ ትንተና የአውሮፓ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን በ1997ቱ የኢትዮጵያ ምርጫ ላይ ሐቀኛ ሪፖርት አላቀረበም የሚል ነው፡፡ በተለይ የምርጫ ታዛቢ ቡድኑን በመሩት ፖርቱጋላዊቷ አና ጎሜዝ ላይ ጠንከር ያለ ተቃውሞን ከመሰንዘር ባሻገር ዘለፋ አከል አነጋገሮችን ተጠቅመዋል፡፡ በኢትዮጵያን ሔራልድ ጋዜጣ ለመጀመርያ ጊዜ በስማቸው ባወጡት ጽሑፍ ቡድኑ በሪፖርቱ ያካተታቸው ጥሬ ሐቆች ያሉት ቢሆንም፣ ድምዳሜው ሁሉ መሠረታዊ ችግር ያለበት መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ በሪፖርቱ በተካተቱ የምርጫ ጣቢያዎች ሁሉ ተስተዋሉ የተባሉትን ችግሮች በዝርዝር በማስታወስ ለችግሮቹ መንስዔ የሆኑትንና ሪፖርቱ በውል ያላጤናቸውን ነገሮች በመዘርዘር የሪፖርቱን ኢ-ሚዛናዊነት ያስቀምጣሉ፡፡ በተለይ በቡድን መሪዋ ላይ ካነሷቸው አበይት ነጥቦች መካከል ግለሰቧ የምርጫውን ሒደት ከመታዘብና ከመዘገብ ኃላፊነት አልፈው በድህረ ምርጫው በተነሱት ያለመግባባት ጥያቄዎች የመፍትሔ ሐሳብ ጠቋሚ ሆነው ቀርበዋል የሚል ነው፡፡ አና ጎሜዝ በሪፖርታቸው ምርጫው በተቃዋሚዎች አሸናፊነት መጠናቀቁን ገልጸው የተጋረጠውን አደጋ መመለስ የሚቻለው መንግሥትና ተቃዋሚዎች ወደ ጥምር መንግሥት የሚያመራቸውን የጋራ ስምምነት ማድረግ ሲችሉ እንደሆነ የሚገልጽ ንድፈ ሐሳብ ነበራቸው፡፡ 
በእነዚህና በሌሎችም ተጨማሪ ጉዳዮች የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ‹‹በሪፖርቱ ያልተካተተ ነገር ግን የሪፖርቱ ችግር ምንጭ›› ያሉት አና ጎሜዝን የሚሸነቁጡ ንግግሮችንና ዘለፋዎችን ሰንዝረዋል፡፡ በምላሻቸው ማጠናቀቂያ ላይ የቡድን መሪዋን የመፍትሔ ሐሳብ ላቅርብ ባይነትን በነገር ሲወጉ ‹‹የተከበሩት ወይዘሮዋ ከምርጫው ጋር ተያያዥነት የለውም ብለው እንጂ ዘንድሮ ስላገኘነው ጥሩ የዝናብ መጠንም አስተያየት መስጠት ይችሉ ነበር፤›› ሲሉ መልሰዋል፡፡ 
ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ምላሽ የብዙዎችን ቀልብ የሳበው በጽሑፋቸው መጨረሻ ያሰፈሩት፣ ‹‹What’s love got to do with it›› የታዋቂዋ አፍሪካ አሜሪካዊት ዘፋኝ ቲና ተርነር ዘፈን ወይዘሮዋን ሸንቆጥ ማድረጋቸው ነበር፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጽሑፍ እስካሁን በወይዘሮዋ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ ከፍተኛ ይመስላል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ኅልፈት ያደረባቸውን ስሜት እስከመግለጽ ደርሰዋል፡፡ 
አና ጎሜዝ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ በእጅጉ መበሳጨታቸውን በመግለጽ ‹‹ከተቃዋሚዎች የገንዘብ ድጋፍ እንደተደረገልኝና ሌላ ሌላ አስመስለው ነው የገለጹኝ፡፡ በጣም ምርጥ ጭንቅላት ያለው ሰው ቢሆንም የሰው ሐሳብ የማምታታት ችሎታ የነበረው መሪ ነው፤›› ሲሉ ነው የገለጿቸው፡፡ 
ቪዛ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ማግኘታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ መሞት ያገናኙት አና ጎሜዝ የብሔር ጉዳይም ማንሳታቸው በኢትየጵያ ስላዩት መሻሻል እንዲነግሩት ለጠየቃቸው አዲስ ስታንዳርድ መጽሔት፣ በሰጡት ምላሽ ‹‹አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሚናውን ለመጫወት ቀላል አይሆንም፡፡ በውስጣቸው የሥልጣን ሽኩቻ እንደነበርም አውቃለሁ፤ እሱ ከትግራይ አይደለማ፡፡ የተሰጠኝን ቪዛ ትልቅ ትርጉም እሰጠዋለሁ፤›› ብለዋል፡፡ 

No comments: